ባህላዊ ጋብቻ

ጋብቻ በጉራጌ ብሔር ከፍተኛ ክብርና ቦታ ያለዉ ማህበራዊና ባህላዊ ክዋኔ ነዉ፡፡ ቀደም ባለዉ ጊዜ ሁለት ተጋቢዎች ለአንድም ቀን ከሰርጋቸዉ እለት በፊት ሳይተያዩ ይጋቡ እንደነበር ይነገራል፡፡ በቀድሞዉና ባሁኑ ወቅት የሚከናወኑ የሰርግ ሂደቶች መካከል የቸግና የሰርግ ስነ-ስርዓቶች እንደሚከተለዉ ቀርቧል፡፡
–
ቸግ( ፍጥምጥም)
ቸግ ማለት (ሽምግልና ወደ የሴቷ ቤተሰቦች የሚላክበት ቀን) ሲሆን ሁለት ተጋቢዎች ሲኖሩ የወንዱ ቤተሰቦች ወደ ሴትዋ ቤተሰቦች ሽማግሌዎችን እስከ ዙር ይልካሉ ። በመጀመርያው የሽማግሌ ዙር ወይም በ2ኛው የሴትዋ ቤተሰብ እሺታን ወይም እምቢታን አይናገሩም። እናስብበት በማለት ለሌላ ጊዜ ቀነ ቀጠሮ ይሰጡና ሽማግሌዎቹን እቤትም ሳያስገቡ ከበር ይመልሱዋቸዋል።ሽማግሌዎቹ በቀጠሮዋቸው መሰረት ተመልሰው የሴቷ ቤተሰቦችጋ ይሄዳሉ ፤ እሺታውን ወይም እንቢታውን ለማወቅ። የሴቷ ቤተሰቦች ለትዳሩ ፍቃደኛ መሆናቸውን ሲያውቁ በሁሉ ነገር እቤት ውስጥ ተዘጋጅተው ይጠብቋቸዋል፣ ሽማግሌዎቹ ሲመጡ አናታቸው ላይ የሚቀመጥላቸው ቂቤም ያዘጋጃሉ።ሽማግሌዎቹ እቤት ገብተው እሺ እስኪባሉ ድረስ ይቆማሉ ፣ አይቀመጡም። እሺ እንደተባሉ ይቀመጣሉ ቂቤ አናታቸው ላይ ተደርጎ በ ጨርቅ ይታሰርላቸዋል።ይኀ ቀን ” #ቸግ” ይባላል። የዛን ቀን ሽማግሌዎቹ እና የ ሴትዋ የቅርብ ዘመዶች ይገኛሉ ። ምግብ ይመገባሉ። ከዚያም ወደ ልጁ ቤት በመሄድ ለሰርግ ዝግጅት እንዲደረግ ያበስራሉ።
አግኖት ወይም አዠመነ ሸባል/ሰርግ/
አግኖት ወይም አዠመነ ሸባል/ሸርግ/ በጉራጌ ብሔር ሌላዉ በጋብቻ የሽግግር ደረጃዎች ዉስጥ የምናገኘዉ ባህላዊ ክዋኔ ነዉ::ዋናዉ የሰርግ እለት ከመድረሱ በፊት ሙሽሪት ሙሽራዉ የሚወጡበትና የሚገቡበትን ቤት ማስዋብና አጥር ማጠር፣ከተጋባዥ እንግዶች ለሙሽራዎቹና ለአጃቢወቻቸዉ የሚሆን ቆጮ የእርድ ከብት ፣ሰኸር(የጉራጌ ባህላዊ መጠጥ)፣ጠላ፣ቂቤ፣ሚጥሚጣ፣ ወ.ዘ.ተ ዋና ዋናዎቹ ለሰርግ የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ቢሆኑም የቅርብ ዘመዶችም እንደየአቅማቸዉ እገዛ ያደደርጋሉ፡፡ በጉራጌ ብሔር አብዛኛዉ ሰርግ የሚከናወነዉ በክርስትና እምነት ተከታዮች የመስቀል በዓልን ተንተርሶ ሲሆን የእስልምና እምነት ተከታይ በሆኑት ደግሞ ከአረፋ በዓል ጋር ተያይዞ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ለዚህ ደግሞ ቀዳሚዉ ምክንያት ተወላጁ ከቆዬዉ ርቆ በተለያ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ በየቦታዉ የሚኖረዉ አብዛኛዉ የጉራጌ ብሔር ወደ ትዉልድ አካባቢዉ የሚሰበሰበዉ በእነኚዉ ሀይማኖታዊ ክብረ-ዓላት ወቅት በመሆኑ ነዉ፡፡




