የፈራ ገዘኘ ሴራ
የመስቃን ቤተ-ጉራጌ የዳኝነት ሴራ።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ባለቤት ናት።እነዚህ ሁሉንም ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶች አላማቸው ለተበደለ ፍትህ ፣ ለተጎዳ ካሳ ፣ መንገድ ለሳተ አቅጣጫ እንዲሁም የህብረተሰቡ የአብሮነትና የአንድነት ብሎም የሰላም አምባሳደር ሆነው የቆሙ እሴቶቻችን ናቸው። የመስቃን ቤተ-ጉራጌ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት በክፍል አንድ እንዳስሳለን።
በአጭሩ ሥልና -ስር ማለት የወንጀለኛና የፍትሀብሔር ጉዳዮችን አካቶ የያዘ የህዝብ መተዳደሪያ ህገ ደንብ / የፈራገዘኘ ሴራ / እንደ ማለት ሲሆንበመስቃን ቤተ-ጉራጌ ውስጥ የስልና ስር ስርዓት ተግባራዊ አተገባበሩ አንድ ሰው በሌላው ሰው የአንድ ሰው እንሰሳ ከሌላው ሰው እንሰሳ እንደዚሁም አንድ ሰው በሌላው ሰው ቡቃያ ላይ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ጉዳት በማድረሱ /ጥፋት በመፈጸሙ/ ሳቢያ በሰዎች መካከል ያለመግባባት ሲፈጠር የተፈጠረውን ቅራኔ ለመፍታት የሚወስደው የመፍትሄ እርምጃ ስልና – ስር ይባላል፡፡ሰዎች በየትኛውም መንገድ በይፋም ሆነ በስውር በእንሰሳት ላይ በእጽዋት ላይ በንብረት ላይ ወዘተ በደል ፈጽመው የፈጸሙት በደል ያለ አግባብ መሆኑ ምስክር ሳያስፈልግ በራሳቸው አንደበት ሲያረጋግጡ ጉዳዩ በባላዊ መንገድ ተመርምሮና ጥፋተኛ የሆነው ክፍል የሚጠየቅበት የህዝብ የፍትህ ስርዓት ሥልና -ሥር ይባላል፡፡ይህ ስልና ስር /ፈራገዘኘ/ በመባል የሚታወቀው የዳኝነት ስርኣት የተለያዩ እርከኖች ወይም ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ዋና ዋናዎች የፍትህ ዘርፎች ሶስት ናቸው፡፡እነሱም1ኛ. ማጋ2ኛ. ራጋ3ኛ. ገፌቻ /ፈራገዘኘ/ ይባላሉ1ኛ. ማጋ፡- የሚባለው የፍትህ ስርዓት በየአካባቢው /በየሰፈሩ/ የሚገኙና በተለያየ ጉዳይ የተበደሉ ሰዎች ቅሬታቸው አዳምጠው መረጃ ሳያስፈልግ በፈራገዘኘ ሴራ መሰረት በማደራደር በጥፋተኛ ወገን ላይ ተገቢውን እርምጃ / ካሳ/ቆርጦ ማስማማት የሚችል የህግ ስርዓት ሆኖ በህዝብ ዘንድ እውቅና ቢኖረውም የታወቀ የማስታረቂያ ቦታ ሳይኖራቸው በየመንገዱ የሚያስታርቁ ሽማግሌዎች ናቸው።እነዚህ የማጋ ሽማግሌዎች ከሞት ጉዳይ በስተቀር ሁሉንም አለመግባባት ፈተው ማስታረቅ የሚችሉ ናቸው፡፡2ኛ.ራጋ፡- ማለት በየሰንጋው / በየጎሳው/ በግለሰብም ሆነ በቡድን በሚከሰቱ ወንጀሎች ሳቢያ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ችግሩ መርምረው በፈራገዘኘ ሴራ መሰረት ምስክር ሳያስፈልግ በዳይ ነኝ የሚለው ወገን እራሱ በራሱ ላይ የሚያቀርበው ጥፋት አድምጦ መፍትሄ ለመስጠት በህዝቡ ተወክለው (እውቅና ተሰጥቷቸው )የተቀመጡ ባህላዊ የፍትህ አካላት ሲሆኑ የሚያስታርቁበት ውስን ቦታም ይኖራቸዋል ፡፡እነዚህ የራጋ ሽማግሌዎች ሞትን ጨምሮ ሁሉንም አለመግባባቶች መፍታት የሚችሉ ሲሆን የጡር ዳኛም ይሰይማሉ፡፡ራጋም ሆነ ማጋ የሚባሉ እነዚህ ባህላዊ የፍትህ አካላት ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት የጀመሩበት ትክክለኛ ጊዜ ለመናገር ቢያስቸግርም ከፈራገዘኘ ሴራ ጥቂት ዘግየት ብሎ እንደነበር አባቶች ይናራሉ፡፡የሴራዎቹ ጥንካሬና ፍትሃዊነት እንደየጎሳውና እንደግለሰቦቹ ጥንካሬ የሚወሰን ቢሆንም የውሪቡ የሼህ/ በርከሌ ረጋ ፣ የዶቢው የኮኮቤ ራጋ፣ የአንቦሩ የሰናኖ ራጋ፣ የእም መስቃን /የአሊሎ ወይም የገበጠማኑ/ ራጋ ፣ የበሬሳው የአዝ/ አጭራምት ራጋ የባቲ ሌጃኖ የሃጂ ኢብራሂም ራጋ በፍትሃዊነታቸውና በጥንካሬያቸው እስከዛሬም በህዝቡ አእምሮ ያልተረሱ የራጋ ቦታዎች ናቸው፡፡3ኛ.ገፌቻ(ፈራገዘኘ)፡- ማለት በመስቃንኛ ቋንቋ ይግባኝ እንደማለት ሲሆን በአካባቢው ይተገበሩ ከነበሩ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ሁሉ ከፍተኛውና የመጨረሻው ፍርድ ሰጪና ይግባኝ ሰሚ የፍትሀ አካል ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ፈራገዘኘ በመባል የሚታወቀው ይህ ባህላዊ የፍትህ አካል የሚቀርቡለትን ቅሬታዎች አጣርቶና መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ጉዳዩ በማጋም ሆነ በራጋ ሽማግሌዎች ሲታይ የነበረበት ሂደት በዝርዝር ካዳመጠ በኋላ በበዳይ ተበዳይ በኩል የተመረጡ ሁለት የጉዳ ዳኞች መኖራቸው /መገኘታቸው/ ማረጋገጥ የበዳይ ተበዳይ ወላጅ አባት በህይወት ካሉ መገኘታቸውና ፣ የሁለቱም ወገን ወንድሞች ካሉ ስለመገኘታቸውና ያለበለዚያም ከሁለቱም በኩል የተገኙ የቅርብ ቤተሰብ አባላት መኖራቸው ያጣራሉ፡፡ወንጀል ፈጻሚው ግለሰብ እራሱ በመምጣት በቅርብ ርቀት መቀመጡን ካረጋገጡ በኋላ ይግባኝ ጠያቂዎች ወይም ሁለቱ ባለጉዳዮች ጉዳያቸውን እልባት እስከሚያገኝ ከፈራገዘኘ ሽማግሌዎች ጋር እንደምን አደራችሁ የሚል ሰላምታ ከመስጠት ውጪ መጨባበጥ መሳሳምና ስለቤተሰብ መጠያየቅ የማይቻል መሆኑ ተነግሮ ወደ ጉዳዩ ይገባል፡፡ሁለቱ የጉዳ ዳኞች በተገኙበት ቅሬታ አለኝ የሚለው ወገን ሀሳብ ያቀረብና የፈራገዘኝ ሴራ (ጉርዝ) የቀረበለት አዳምጦ በማመዛዘን ውሳኔውን ሊቀንስ ወይም ሊጨምር አልያም እንደነበረ በማጽደቅ አስማምቶ ሊሸኝ ይችላል፡፡
ይበልጥ ያንብቡClose





