የመስቀል በዓል
የመስቀል በዓል ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ንግሥት እሌኒ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ ካስወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡ ንግሥቲቷ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ቂራቆስ በተባሉ አባት ጠቋሚነት ለማግኘት ደመራ አስደምራ ፍለጋ የጀመረችው መስከረም 17 ቀን እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡የሃይማኖት አባቶችን አሰባስባ በፀሎት እንዲረዷት ጠይቃ፣ ከደመራው በሚወጣው ጢስ ጠቋሚነት መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ አግኝታለች፡፡ መስቀሉም ከወራት ቁፋሮ በኋላ ወጥቷል፡፡ ከዚያን ወቅት ጀምሮ መስከረም 16 ቀን የደመራ ሥነ ሥርዓትና መስከረም 17 የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ እንዳለ ሆኖ በየአካባቢው እንደየማኅበረሰቡ ባህልና ወግም ይከበራል፡፡ ከሌሎች ዐውደ ዓመቶች የመስቀል በዓል በተለየ በድምቀት በሚከበርባቸው አካባቢዎች የብዙ ጎብኚዎችን ትኩረትም ይስባል፡፡ በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ በዓለም ቅርስነት የሰፈረውም ለዚሁ ነው፡፡
በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል ትልቁና ዋንኛው የመስቀል በዓል ነው፡፡ የመስቀል በዓል በጉራጌ ብሔረሰብ ያለው ማህበራዊ ፋይዳ ዓመቱን ሙሉ ተለያይተው የኖሩ ቤተሠቦችና ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የሚጠያየቁበት፣ ማህበራዊ ችግሮቻቸው የሚፈቱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሠቦች የሚጠያየቁበት፣ የተጣሉ ሠዎች የሚታረቁበት፣ እዳ የሚሠረዝበትና በዳይና ተበዳይ ይቅር የሚባባሉበት በዓል ነው በዓሉን ከቤተሰባቸው ጋር በማክበራቸው ምርቃትና በረከትን ይቀበላሉ።
የመስቀል_በዓል የዝግጅት ሁኔታዎች
የመስቀል በዓል ዝግጅት የሚጀምረው መስቀል በተከበረበት ማግስት ጀምሮ ለሚቀጥለው አከባበር ማሠብ ይጀመራል፡፡ መስቀል ሶስትና አራት ወራት ገደማ ሲቀሩት ዝግጅቱ እየተጧጧፈ ይሄዳል፡፡ በዚህ ወቅት የሥራ ክፍፍሉ በዕድሜና በፆታ እንደየ አቅሙና ችሎታው ይሠጣል፡፡አባት በወንድ ልጆቹ እየታገዘ በበጋው ወቅት ለመስቀል የሚሆን በቂ የማገዶ እንጨት ያዘጋጃል። ቤቱ አርጅቶ ከሆነ ይጠግናል። በዓሉ ሲቃረብም በከተሞች ከሚኖሩ ልጆቹና ወንድሞቹ በሚላክለት ገንዘብ ካለዚያም በራሱ ወጭ የመስቀል የእርድ ከብት ይገዛል።
እናት ደግሞ በሴት ልጆቿ እየታገዘች ለመስቀል የሚያስፈልገውን ቆጮ፣ ቅቤ፣ ቡላ፣ አይብ፣ ጎመን፣ ሚጥሚጣ፣ ቅመማቅመሞች ታዘጋጃለች። ሴት ልጆች ቤቱንና ደጁን ያሳምራሉ። ግድግዳውን የባህል ቀለም በጥብጠው በማዘጋጀት ይቀባሉ። መስቀል በጉራጌ አስቀድሞ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ከተደረገበት በኃላ በዓሉ ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጀ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች እየተጠቀሙ በታላቅ ደስታና ጭፈራ እንዲሁም ልዩ ልዩ ክንዋኔዎችን በማካሄድ የሚከበረ ሲሆን የቀናቶቹ ስያሜና የሚካሄዱ ተግባራት እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
